+251 911 02 84 09
Staff Login
Logo

Gedeo Zone Finance & Plan Department

የጌዴኦ ዞን ፋይናንስና ፕላን መምሪያ

Official Government Portal

የመንግሥት መረጃ ፖርታል

economy

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) በነገው ዕለት መላው ህብረተሰብ አረንጓዴ አሻራቸውን እንዲያኖሩ መልዕክት አስተላለፉ

August 03, 2026 1 Views
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ  ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) በነገው ዕለት መላው ህብረተሰብ አረንጓዴ አሻራቸውን እንዲያኖሩ መልዕክት አስተላለፉ
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) በነገው ዕለት መላው ህብረተሰብ አረንጓዴ አሻራቸውን እንዲያኖሩ መልዕክት አስተላለፉ

‎(#ዲላ ሐምሌ 26-2018 ዓ/ም) በነገው ዕለት በመላው ሀገሪቱ በሚካሄደው የአንድ ጀንበር 800 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር መላው ህብረተሰብ አረንጓዴ አሻራቸውን እንዲያኖሩ መልዕክት አስተላልፏል።

‎ ለዚህ ታላቅ ሀገራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ መላው የጌዴኦ ዞን ህብረተሰብ በነቂስ ወጥቶ በመሳተፍ አሻራውን እንዲያኖር አስተዳዳሪ ጥሪ አቀርበዋል።

‎አስተዳዳሪ በመልዕክታቸው እንደገለጹት፣ የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን አካባቢያዊ ዘላቂነት ለማረጋገጥ፣ የደን ሽፋንን ለማሳደግ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም፣ የውሃና የአፈር ሀብትን ለመጠበቅ እንዲሁም ለቀጣይ ትውልድ አረንጓዴና ለምለም ኢትዮጵያን ለማስረከብ የሚደረግ ታሪካዊ ሀገራዊ ጥረት መሆኑን ገልጸዋል።

‎በመርሃ ግብሩ መሠረት ጌዴኦ ዞን በአንድ ጀንበር 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅቱን መጠናቀቁን የጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው፣ ይህን ግብ በተሳካ ሁኔታ ለማሳካት ሁሉም የዞኑ ነዋሪዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ አርሶ አደሮች፣ ተማሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሲቪል ማኅበራት እና ሁሉም ባለድርሻ አካላት በአንድነት በመንቀሳቀስ በተዘጋጀው ሥፍራ የችግኝ ተከላ ተገኝተው እንዲያከናውኑ አሳስበዋል።

‎"ዛሬ የምንተክለው ችግኝ የነገው የህይወት ዋስትና ነው። ለልጆቻችን እና ለሀገራችን ዘላቂ ሀብት የምንተወው አሻራ ነው። ስለዚህ ሁሉም የጌዴኦ ዞን ነዋሪዎች በነቂስ ወጥቶ በመሳተፍ የዞናችንን እና የሀገራችንን የአረንጓዴ አሻራ ጉዞ ከፍ" እናደርግ ሲሉ ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር) አሳስበዋል።

‎ዋና አስተዳዳሪው አክለውም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከችግኝ ተከላ በላይ የሀገር ፍቅርን፣ የትውልድ ኃላፊነትን እና የጋራ ልማት ባህልን የሚያጠናክር ሀገራዊ እንቅስቃሴ መሆኑን በመግለጽ፣ በነገው ዕለት በጌዴኦ ዞን የሚተከሉት 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ችግኞች ለዞኑ የአካባቢ ጥበቃ፣ ለግብርና ልማት፣ ለቡና ምርት ዘላቂነት እና ለአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።

‎በመጨረሻም መላው የጌዴኦ ዞን ህብረተሰብ በታላቅ ሀገራዊ መንፈስ ተነሳስቶ በነገው ዕለት በሚካሄደው የአንድ ጀንበር 800 ሚሊዮን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በንቃት በመሳተፍ የራሱን የአረንጓዴ አሻራ እንዲያኖር ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

‎@የጌዴኦ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት!
Share this article: